አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞሮኮ ራባት እየተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም ጎን ለጎን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በኢትዮጵያ እና በባንኩ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሦስት ስትራቴጂያዊ የትብብር መስኮች ላይ ትኩረት አድርገው ባደረጉት ምክክር፥ ኢትዮጵያ የምታስተናግደውን 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ32) መደገፍ ስለሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረዋል።
በተጨማሪም የባንኩ ድጋፍ ስለሚጠናከርበት ሁኔታና የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ከፍተኛ ውጤት በሚያመጡ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ በዚሁ ወቅት፥ ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትንና አካታች ዕድገትን ለማስቀጠል ኢትዮጵያ ከባንኩ ጋር ያላት ወሳኝ አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ባንኩ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት የበጀት ድጋፍ ማሰባሰብና ለኮፕ32 ቅድመ ዝግጅት ላሳየው አጋርነት ኢትዮጵያ ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች ነው ያሉት፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ሲዲ ኡልድ ታህ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኢትዮጵያ የሪፎርም ስራዎች ያመጡትን ውጤት አድንቀው፥ ተቋማቸው በግል ኢንቨስትመንት፣ በማክሮኢኮኖሚ ማረጋጋትና ቀጣናዊ ትብብርን በማሳደግ ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ዝግጁነቱን አረጋግጠዋል።

