አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 14 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጣ የነበረ 449 ሺህ 700 የአሜሪካ ዶላር መያዙን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ገንዘቡ የተያዘው በሁመራ መስመር በሦስት የኢትዮጵያ ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች ከሀገር ለማስወጣት ሲሞከር መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም በወቅታዊ ምንዛሪ ተመን 17 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር ዋጋ ያለው ገንዘብ እና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ የተጠረጠሩ ሶስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተጠርጣዎቹ ገንዘቡን ከሀገር ለማስወጣት የሞከሩት በሁመራ ጉምሩክ መቅረጫ ጣቢያ የሊጉዲ መቆጣጠሪያ ጣቢያን ወደ ጎን በመተው በጫካ በመጓዝ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩን በመከታተልና በመያዝ የሁመራ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሰራተኞች፣ የመከላከያ ሰራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ አባላት ከፍተኛ ሚና ነበራቸውም ነው የተባለው።
የተያዘው ገንዘብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ መደረጉን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

