አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሆንግ ኮንግ የ128 ሰዎችን ሕይወት ከቀጠፈው የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ተጨማሪ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የሀገሪቱ ገለልተኛ የጸረ ሙስና ኮሚሽን (ICAC) እንዳስታወቀው÷ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከአደጋው በፊት ሲከናወን ከነበረው የህንጻዎች መልሶ ጥገና ሂደት ጋር በመጠርጠራቸው ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ጥገናውን የሚያካሂደው የኢንጂነሪንግ ኩባንያ ዳይሬክተርን ጨምሮ የንዑስ ኮንትራክተሮች ሰራተኞች እንዳሉበት ተነግሯል።
የአደጋውን መድረስ ተከትሎ ቀደም ሲል ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ አሁን ላይ ተጨማሪ ስምንት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደ ይገኛል።
የደረሰው ከባድ አደጋ መንስኤው ምን እንደሆነ እስካሁን በግልጽ ባይታወቅም ለህንጻው መልሶ ጥገና ተብሎ ተወጥሮ የነበረ ተቀጣጣይነት ያለው የፕላስቲክ መረብ አደጋውን አስከፊ አድርጎታል።
የአደጋውን ምክንያት ለማጣራት ፖሊሶች ወደ ህንፃው በመግባት ምርመራ እያደረጉ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ ተመላክቷል፡፡
በሆንግ ኮንግ ባለፈው ረቡዕ በጋራ መኖሪያ ቤት ሕንጻዎች ላይ በተከሰተው የእሳት አደጋ 128 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይ ሰዎች ደግሞ እስካሁን የገቡበት አልታወቀም ተብሏል፡፡
ከ4 ሺህ 600 በላይ ሰዎች በሚኖሩባቸው ሕንጻዎች የተከሰተውን የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለ ሲሆን በክስተቱ ላይ የሚደረገው ማጣራት እንደቀጠለ ነው፡፡
የሆንግ ኮንግ የደህንነት ኃላፊ ክሪስ ታንግ÷ አደጋውን ለመቆጣጠር ከ2 ሺህ በላይ የእሳት አደጋ ሰራተኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
አደጋው ከመድረሱ በፊት ሁሉም ሕንጻዎች ላይ የተገጠሙ የእሳት አደጋ የጥንቃቄ መልዕክት መሳሪያዎች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልነበር መጠቆማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ

