አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰጠው ልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለ30 ሺህ የከተማችን ወጣቶችና ሴቶች በዛሬው ዕለት አዲስ የስራ ዕድል ፈጥረናል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንድ ጀምበር ለ30 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄን አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፥ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
ዛሬ የምንገነባው ትውልድ በክህሎትና በዕውቀት የበለጸገና ችግር ፈቺ እንዲሆን እየተጋን ነው ያሉት ከንቲባዋ፥ በአንድ ጀምበር ለ30 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግብር የዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህም ወጣቶች ከዛሬ ጀምሮ በከተማ ግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በአምራች ዘርፎች ስራ ይጀምራሉ ነው ያሉት።
በመዲናዋ የሚፈጠረው የስራ ዕድል ፈጠራ የስራ ገበያው በሚፈልገው ልክ እንዲሆን ለወጣቶች ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ከንቲባዋ ለወጣቶቹ የስራ መሳሪያዎችን ያበረከቱ ሲሆን፥ በቀጣይም በሚሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው፥ በመዲናዋ የስራ አጥነትን ለመቀነስና ለስራ ዕድል ፈጠራ ያሉ ጸጋዎችን በጥናት በመለየት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ለ366 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን አስታውሰው፥ በ2018 ባለፉት አራት ወራት ብቻ ለ158 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በመዲናዋ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የብድርና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ለማመቻቸት ከተማ አስተዳደሩ እየሰራበት እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
በመዲናዋ ለክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው፥ በ14 የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ወጣቶችን በማሰልጠን የስራ ዕድል እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ በሚገኘው የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በመሳፍንት እያዩ

