Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከአየር መንገድ ደህንነት ጋር ተያይዞ በወንጀል የተከሰሱት እነ ዮሃንስ ዳንኤል ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ደህንነት ጋር ተያይዞ በወንጀል የተከሰሱት እነ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) በእስራት እንዲቀጡ ወስኖ  የታሰሩት በቂ ስለሆነ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጠ።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ እና ይዲድያ ነጻነት ላይ በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሰዓት ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቐለ ከተማ ለመጓዝ አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ ቢሆንም የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች በመሆኑ በረራው ቢደረግ የሚያደርሰውን ከባድ አደጋ ለመከላከል ጉዞው ተሰርዞ መንገደኞች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ሲነገራቸው በረራው በግድ መደረግ አለበት አንወርድም በማለት ቀሪ ተሳፋሪዎችም እንዳይወርዱ በመክልከል አሳድመዋል በሚል በዝርዝር ጠቅሶ ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ 1ኛ ተከሳሽ ጆን ዳንኤል ላይ በ3ኛ ክስ የኮምፒዩተር ወንጀል ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 3 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ክስተቱን ቲክቶክ በተባለ ማህበራዊ ሚዲያ በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርጾ በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ የሚል ክስ አቅርቦበት ነበር።

ተከሳሾቹ በተከሰሱበት የህግ አንቀፅ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን ችሎቱ በዛሬው ዕለት የዐቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃ እና የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ተከሶሾቹ የተከሱበት የህግ አንቀፅ ቀላል እስራትን የሚያስከትል በመሆኑ 1ኛ ተከሳሽ በአንድ አመት ከአራት ወር፤ 2ኛ፣ 3ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በስምንት ወር እንዲሁም 4ኛ ተከሳሽ በ10 ወር እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

በመሆኑም ተከሳሾቹ በእስር ላይ የቆዩበት ጊዜ ተሰልቶ ተከሳሾቹ እንዲፈቱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ልዩ ልዩ ከባድ ወንጀል ችሎት ውሳኔ አሳልፏል።

በሲፈን መኮንን

Exit mobile version