Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለትግራይ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን አስመልክቶ ለትግራይ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበራት ህብረት የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በዚህም ከ7 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ዊልቼር፣ ክራንች፣ መስማትን የሚያግዙ መሳሪያዎች፣ ነጭ በትሮች እና ሌሎች ቁሳቁሶች የተበረከቱ ሲሆን፤ ተጨማሪ 700 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ድጋፉ የክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበራትን ለማጠናከር ይረዳል።

ከዚህ በፊት ለማህበራቱ ድጋፍ መድረጉን አስታውሰው፤ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው በክልሉ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ጠቅሰው፤ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን በክልሉ ለማክበር ለተገኙ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በክልሉ አካል ጉዳተኞችን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማካተት እና እኩል ተሳታፊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዕለቱን ስናከብር ከዚህ በኋላ የአካል ጉዳትን በማይፈጥሩ አማራጮች ላይ በማተኮር ሊሆን ይገባል ያሉት ደግሞ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ዶ/ር) ናቸው።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ሂዳያ አሊ ግጭት እና ጦርነት አንዱ የአካል ጉዳተኝነት ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰላምን ለማጽናት መሰራት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን እና ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፉን ማሰባሰቡ ተገልጿል።

Exit mobile version