አዲስ አበባ፣ ሕዳር 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየሰራሁ ነው አለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ።
የንግድ ቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ በከተማዋ የዘይት አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠርና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
የዘይት ምርት በሀገር ውስጥ በበቂ ሁኔታ መኖሩን የጠቀሱት ኃላፊዋ÷ አንዳንድ የከተማዋ ነጋዴዎች የምርት እጥረት እንዳለ በማስመሰል ዋጋ ለመጨመር ይሞክራሉ ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሸማች ማህበራት፣ በአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት በኩል 5 ሊትር ዘይት በ1 ሺህ 400 ብር ለተጠቃሚዎች እየቀረበ መሆኑን ጠቁመው ÷ ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች ከዚህ በላይ በሆነ ዋጋ ሲሸጡ እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል፡፡
ቢሮው በሸማች ማህበራት፣ በችርቻሮ እና በተቋማት በኩል የዘይት ምርት በበቂ ሁኔታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ እንደሚገኝ ሃላፊዋ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለአብነትም በአዲስ አበባ ንግድ ሥራዎች ድርጅት በኩል የዘይት፣ ጤፍ፣ ፓስታ፣ ፉርኖ ዱቄት፣ ማካሮኒና ሌሎች የፍጆታ ምርቶችን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በከፈታቸው መጋዘኖቹ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
ጋርመንት አካባቢ የሚገኘው የድርጅቱ የሽያጭ ኃላፊ አቶ ደንደና ዱጉማ የድርጅቱ ዋና ዓላማ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት መሆኑን ገልጸው ÷ በጅምላ ከማከፋፈል ባለፈ በችርቻሮ መልክም በቀጥታ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
ተቋሙ በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች መጋዘኖችን በመክፈት እንደ ዘይት፣ ስንዴ፣ ጤፍ ፣ ማካሮኒ፣ ፓስታና ሌሎች ሸቀጦችን በጀሞ፣ ለገሃር፣ አቃቂ፣ ቤተል እና ለሚ ኩራ አካባቢ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የንግድ ቢሮ የምርት እጥረት እንዳይፈጠር፣ ሲፈጠርም ፈጥኖ በመፍታት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን የማረጋጋት ሚና እየተወጣ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ አስገንዝበዋል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ

