Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከ4 ዓመታት በኋላ ሕንድን የሚጎበኙት የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን…

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሕንድ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ኒው ዴልሂ አቅንተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሀገራቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትብብሮችን ጨምሮ በተለያዩ የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ የብሪክስ አባል ሀገራት ከመሪዎቹ ውይይት ጎን ለጎን በተለያዩ ዘርፎች የመግባቢያ ሰነዶችንና የንግድ ሥምምነቶችን እንደሚፈራረሙ የሩሲያ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል፡፡

ሩሲያ በፈረንጆቹ 2030 ከህንድ ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ 100 ቢሊየን ዶላር የማድረስ ፍላጎት ያላት ሲሆን፥ ሁለቱ ሀገራት በየፊናቸው በሚያቀርቧቸው ተጨማሪ ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፎች ላይ እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡

በዛሬው ዕለት ሕንድ እንደሚገቡ የሚጠበቁት ፕሬዚዳንት ፑቲን ከኢንዲያ-ቱደይ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፥ ከሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጦች 90 በመቶ የሚሆነው በራሳቸው የመገበያያ ገንዘብ አማካኝነት የተከናወነ ነው፡፡

ሞስኮ እና ኒው ዴልሂ ህጋዊ ጥቅሞቻቸውን ከማስጠበቅ ውጪ ከየትኛውም ሀገር ጋር ወደ ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የላቸውም ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version