Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠው የሰላም ስምምነት …

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠ ነው አሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባለት።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና አፋህድ መካከል በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነትና አስተባባሪነት የዘላቂ ሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወቃል።

የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፤ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የምትገልጸውን የአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት መርህ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፤ አለመግባባቶችን በውይይትና ድርድር መፍትሔ መስጠት የሰለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት መገለጫ ነው ብለዋል።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአፋህድ መካከል የተደረሰው የዘላቂ ስምምነትም ሰላምን የሚያጸና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ የውጭ ኃይሎችን ሴራን በማክሸፍ ህዝብ የልማት ሥራውን የሚያፋጥንበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አፍሪካ እንደ አህጉር ሁለንተናዊ ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የዕድገት ጉዞን ለማደናቀፍ የማይሸረብ ሴራ እንደሌለ በመገንዘብ ሁሉም ለሰላም መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን በበኩላቸው፤ የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጥሪ መልስ የሰጠ አስደሳች ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የአፋህድ የሰላም አማራጭ ቁርጠኝነት ለአማራ ህዝብ እፎይታን የሚሰጥና በትጥቅ ትግል ላይ ለሚገኙ ኃይሎች ትምህርት የሚሰጥ አርዓያነት ያለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ ሁሉንም ወገን አሸናፊ ያደረገ፤ ለዜጎች የሰላም ፍላጎት ምላሽ የሰጠ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎችም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን ተቀዳሚ አማራጫቸው ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

Exit mobile version