አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሲደረግ የነበረው የሠላም ድርድር ተቋጫቶ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ፈርመናል፤ ህዝቡም እፎይ ብሏል አሉ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ።
አፋህድ ከመንግሥት ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በወቅቱ፤ ትግሉ የታሰበውን የህዝብ አጀንዳ ከማስመለስ ይልቅ ህዝብና ሀገርን ጥቅም የሚጎዳ፣ ታሪክንም የሚክድ መሆኑን ተረድተን ከመንግሥት ጋር ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል።
የነበረው ትግል ሀገርን ጉዳት ላይ የጣለ በመሆኑ በቀጣይ መንግሥት በሚያደርገው የሰላም ማስከበር ስራ አፋህድ ከጎን እንደሚቆም ገልጸው፤ በጫካ ያሉ አባላት ወደሰላም እንዲመለሱ አብረን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል::
በትግሉ ወቅት በእስር ላይ ያሉ የፋኖ አባላት እንዲፈቱና ወደ ቀደመ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ፣ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የቡድኑ አባላት የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙና በመልሶ ማቋቋም ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከቡድኑ ጋር ሲዋጉ የነበሩ አካላት ወደ ፀጥታ አካላት ገብተው የሀገራቸው ፀጥታ አስከባሪ ሆነው እንዲቀጥሉ ስምምነት የተደረሰባቸው ዋና ነጥቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም በስራና በትምህርት የቆዩ ነገር ግን ቀደም ሲል በውጊያ ሲሳተፉ የነበሩ አካላት ወደነበሩበት ተግባራቸው እንዲመለሱ የሚሉ ስምምነቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።
ለሀገር ግጭትና ጦርነት ሳይሆን ሰላምና አብሮነት እንደሚበልጥና በአብሮነት ለዕድገቷ መቆምና መዋደቅ እንደሚገባ አምነንበት ከመንግስትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጭምር ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አስቀድሞ የነበራትን ብሔራዊ ጥቅም ለመከላከልና ለመቀማት የሚጥሩ ታሪካዊ ጠላቶችን መታገል እንደኢትዮጵያዊ በጋራ የምንሞትለት ጉዳይ ነው ያሉት ካፒቴን ማስረሻ::
የኢትዮጵያን ማደግና መበልፀግ የማይፈልጉ አካላት በርካታ አጀንዳዎችን በመጠንስሰ ቢሰሩም አይጠቀሙም በማለት ገልጸዋል።
የህዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱለትና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ከዚህ በኋላ በግጭት ሳይሆን እንደማህበረሰብ በጋራ ከተንቀሳቀሰን የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ ይቻላል ነው ያሉት።
የሚደረጉ ድርድሮች ሀገር ማሳካት የምትፈልገውን ግብ ለማገዝ የተደረገ ያሉት ደግሞ የአፋህድ መረጃና ደህንነት ኃላፊ መስፍን አባተ ናቸው።
በሀሰት የሚደረግ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ጠቁመው፤ ዘመቻው ኢትዮጵያን በራሳቸው ልክ ማፍረስ የሚፈልጉ አካላት ሴራ ነው ብለዋል።
ትግላችን የአማራና የኢትዮጵያ ህልውና ይከበር ከሚል የመጣ ነው በማለት ገልጸው፤ በሀሰተኛ መረጃና በሴረኞች ድጋፍ አሁንም በፋኖ ስም ሀገርን የሚበጠብጡ አካላት አሉ ነው ያሉት።
የህልውና፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የህገ መንግሥት፣ የማንነትና የወሰን፣ የተፈናቃዮች ትኩረትና ሌሎች የሀሰት ትርክቶች የትግሉ ምክንያቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
እንዲሁም በተራና ጊዜያዊ ጥቅም ላይ የተመሰረቱ አካላት ከመንግስት ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ሀሰት አድርገው ለህዝቡ ለማሳየት እየሰሩ እንደሆነ አንስተው፤ ህዝቡ ይህን ተረድቶ ከሰላም ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሰማኸኝ ንጋቱ

