አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ከልማት ስራዎች ባሻገር ለህዝቦች ትስስርና ለጋራ ትርክት ግንባታ መሰረት የጣልንበት ነው አሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ 20ኛውን የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ከሕዳር 25 ቀን 2018 ጀምሮ በዓሉ በተለያዩ ስያሜዎች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
በዓሉን በስኬት ለማጠናቀቅ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መሰራታቸውን አስታውሰው፤ ዛሬ የክልሉን ፀጋ ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገው “የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀን” እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ነገ ደግሞ የምክክር ቀን ተብሎ በመሰየሙ ሀገራዊ ይዘት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የምክክር መድረኮች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል፡፡
ከነገ በስቲያ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የአደባባይ በዓል የሚቀጥል ሲሆን በዓሉ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር አመልክተዋል።
ቀደም ሲል የነበሩ ትርክቶች ሚዛን ያልጠበቁና ኢትዮጵያዊነትን የማያገዝፉ እንደነበሩ አስታውሰው÷ አሁን ላይ ያሉ ትርክቶች አንድነትን የሚያጎሉና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የዚህ የጋራ ትርክት ውጤት አንድነት፣ ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ ማስቻል መሆኑንም አመልክተዋል።
በማርታ ጌታቸው

