Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሰላም ስምምነቱ ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር እድል የሚሰጥ ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል መንግስት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት (አፋህድ) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የአማራ ህዝብ ከጦርነት ወጥቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር እድል የከፈተ ነው አሉ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ፀጥታ ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ የሰላም ስምምነቱ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የታዩች ችግሮች በርካታ ጉዳት ማስከተላቸውን ጠቅሰው÷ ስምምነቱ በንብረት እና በሰው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ የሚያስቀር ነው ብለዋል፡፡

የበርካታ ቱሪዝም እና ታሪካዊ ቅርሶች መዳረሻ የሆነው ክልሉ በነበረው ግጭት የቱሪዝም ዘርፉ መጎዳቱን አስታውሰው÷ ሰላምን ለማጽናት የሚደረገው ጥረት የቱሪዝም ዘርፉን ጨምሮ ኢኮኖሚውን እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ የአማራ ክልል ለሀገር የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ትስስር በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ሴነሳ ደምሴ ናቸው።

በተለያየ ጊዜ የተደረጉ የሰላም ስምምነቶች ህዝቡ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር እድል የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።

የትጥቅ ትግል ዘመኑን የሚመጥን የፖለቲካ ግብ ማሳኪያ መንገድ እንዳልሆነ አስገንዝበው÷ በሰጥቶ መቀበል መርህ የፖለቲካ ልዩነቶችን በንግግር መፍታት የተሻለ አማራጭ መሆኑን አፅዕኖት ሰጥተዋል፡፡

የተደረጉ ስምምነቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ሌሎች ሀይሎችም ሰላምን አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

መንግሥት፣ ቀጣናዊ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻዎች ሰላምን ለማጽናት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version