አዲስ አበባ፣ ሕዳር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደህንነት አገልግሎት የሚውል የሩት ሰርተፊኬት ባለስልጣን አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል፡፡
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ እንዳሉት÷ አገልግሎቱ ለዜጎች የሚሰጠው እያንዳንዱ ዲጂታል መታወቂያ ትክክለኛ፣ ሊረጋገጥ የሚችልና ሕጋዊ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ያስችላል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚውሉ ዲጂታል ሰርተፊኬቶችን ለማምረት እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡
የአገልግሎቱ መጀመር ኢትዮጵያ ለእያንዳንዱ ዜጋ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ እምነት የሚጣልበትና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል አገልግሎት ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት አገልግሎቱ በይፋዊ ቁልፍ መሰረተ ልማት ውስጥ የደህንነት ማስጠበቂያ ዲጂታል ቁልፎች የሚፈጠሩበትና የሚንቀሳቀሱበት ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ቁልፎች በዲጂታል መታወቂያው ላይ ያለውን የማንነት መረጃ ለመጠበቅ ጥቅም ላይ የሚውል የመተማመኛ ዲጂታል ፊርማ ለማዘጋጀት ያስችላሉ ነው ያሉት።
የብሔራዊ መታወቂያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ አርዓያስላሴ በበኩላቸው÷ አሰራሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ የብሔራዊ መታወቂያን ተዓማኒነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ አብራርተዋል፡፡
የዲጂታል ሰርተፊኬት አገልግሎት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በከፍተኛ ዓለም አቀፍ የደህንነት ደረጃዎች ባላቸው ቴክኖሎጂዎች የተጠበቀ እንዲሆን ሚናው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በጤና፣ ትምህርት፣ ባንክና ሞባይል አገልግሎቶች እንዲሁም ለማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ደህንነቱ የተጠበቀ ፈጣን አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ያስችላል።
የማንነት ስርቆትን፣ ትክክለኛ ግለሰብን የማስመሰል፣ የማጭበርበር እና የማንነት መረጃን ያለአግባብ መጠቀምን ለመከላከል እንደሚረዳም ነው ያስገነዘቡት፡፡
በመላኩ ገድፍ

