Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የፖለቲካ ሽግግር ስኬታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ልትካፈል ይገባል- ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችውን የፖለቲካ ሽግግር ስኬታማ ለማድረግ የሌሎች ሀገራትን ተመክሮ መካፈል እንደሚገባ ፋና ብሮድካሰቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የህግና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ።
 
በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራኑ፥ ሀገራት ካለፉባቸው የሀገረ መንግስት ግንባታ ችግሮች እና ያልተቃኑ የቤት ስራዎች አንጻር በሽግግር ወቅት አለመረጋጋት ሊበረታባቸው እንደሚችልም የተለያዩ ሃገራትን ተሞክሮ በዋቢነት ያነሳሉ ፡፡
 
በአለም አቀፍ እና ሽግግር ፍትህ ላይ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ረዳት ፕሮፌሰር ማርሸት ታደሰ፥ ኢትዮጵያ ብዙ የሽግግር እድሎች አጋጥመዋት ሳትጠቀምበት ቀርታለች ይላሉ።
 
ሽግግር ሲባል መጥፎ ከሚባል አገዛዝ ወደ ጥሩ ወይም ዴሞክራሲያዊ ወደ ሚባለው መንገድ ማዝገም እንደሆነ የሚያብራሩት ረዳት ፕሮፌሰር ማርሸት ታደሰ፥ እነዚህን እርምጃዎች ጀምረናቸው አንድ ወደ ፊት ሁለት ሶስት ጊዜ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሰናል ይላሉ።
 
የተለያዩ ጉዳዮችን አስመልክቶ ያለን እይታ ልዩነት ጫፍ የደረሰ መሆኑ በሽግግር ወቅት ግጭቶች እንዲባባሱ እያደረጉ ስለመሆኑም ያስረዳሉ።
 
ልዩነቱ መሰረታዊ ሆኖ አይደለም የሚሉት ምሁሩ፥ የመነጋገር እና ጉዳዮችን በስርአትና በቅንነት የመፈተሸ ችግር በመኖሩ እንደሆነ ያምናሉ።
 
በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ሞገሰ ደምሴ በበኩላቸው፥ የፖለቲካ ማሻሻያ የሚያደርጉ ሀገራት በተቋም ግንባታ ላይ የሚያጋጥማቸው የቤት ስራ፣ ህግ እና ስርአትን ለማስከበር ፈተና እንደሚሆንባቸው ያነሳሉ።
 
መንግስት የሚያስባቸውን ሃገራዊ እቅዶች ለማሳካት ግን በተለይም ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋም ግንባታው ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያነሱት ምሁራኑ፥ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የግጭቶችን ዋና መንስኤ በጊዜ ሂደት መፍታት እንደሚገባ ያምናሉ።
 
የደቡብ አፍሪካ እና የጋናን የሽግግር ወቅት ልምድ የሚያነሱት የህግ ምሁራኑ፣ ሃገራቱ ያለፉበትን መንገድ መፈተሻቸውና መላ ማበጀታቸው፣ ያለፉ ችግሮችን እያነሳ ግጭት የሚቀሰቅስ ፖለቲከኛን እንደቀነሰላቸውም ተናግረዋል።
 
ይሕ አካሄድ ደግሞ የተፈፀሙ ጉዳዮች ላይ መተማመን እንዲፈጠር ብሎም ዜጎች ይቅር ተባብለው ወደ ፊት እንዲሄዱ የሚያግዝ መሆኑንም በመጠቆም።
 
የሃገር ሰላም እና የዜጎችን ደህንነት የሚያናጋ ነገር ሲኖር ህግ የማስከበሩን ስራ ማስቀጠል ለነገ የሚተው የቤት ስራ አለመሆኑንም ምሁራኑ ተናግረዋል ።
 
በአወል አበራ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

Exit mobile version