አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡን ተከትሎ የወላይታ ዞን ነዎሪዎች ደስታቸውን በአደባባይ እየገለጹ ነው፡፡
በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ ጉባዔ ላይ “ጊፋታ” በሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ዝርዝር ስር ተመዝግቧል።
ይህንኑ ተከትሎም በወላይታ ዞን እና ሶዶ ከተማ እንዲሁም በገጠር አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
በዚህ ወቅትም በርካታ ጠቃሚ እሴቶችን የያዘውን ጊፋታ ጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ገልጸዋል።
የተጣላና የተኮራረፈው የሚታረቅበት የሕዝቦች አንድነትና አብሮነት ይበልጥ የሚጠናከርበትን የወላይታ ዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በማቴዎስ ፈለቀ

