Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሮዛሪዮ ለዓለም ያበረከትችው ባለ ትንንሽ እግሮቹ ንጉስ ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ…

አዲስ አበባ፣ ታሕሳስ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በረገጠበት ቦታ ሁሉ ክብረ ወሰን መስበር የማይታክተው አርጀንቲናዊ ጥበበኛ ሊዮኔል ሜሲ የተወለደው በፈረንጆቹ 1987 በደቡብ አሜሪካዊቷ ሀገር አርጀንቲና ሳንታ ፌ ግዛት ሮዛሪዮ ነው፡፡

ከሮዛሪዮ የተገኘው ትንሹ ልጅ እስከዛሬም ድረስ የዓለም እግር ኳስ ቁንጮ እና አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

በአሜሪካ ለኢንተር ማያሚ እየተጫወተ የሚገኘው ሊዮ ሜሲ በሜጀር ሊግ ሶከር ታሪክ በተከታታይ ሁለት ዓመታት የሊጉ የአመቱ ኮከብ ተጫዋች በመባል ለቁጥር በሚታክቱ ሌሎች ክብረ ወሰኖቹ ላይ አዲስ ክብረ ወሰን ጨምሯል፡፡

ሜሲ ገና በልጅነት እድሜው ወደ ስፔን በማቅናት በ13 አመቱ ላማሲያ አካዳሚን በመቀላቀል ነው የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው፡፡

የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ የሆኑት ሜሲ እና ባርሴሎና በጋራ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገቡ ሲሆን፥ ሜሲ ለካታላኑ ክለብ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሰለፍ ጨዋታውን አድርጎ የነበረው በፈረንጆቹ 2004 በ17 አመቱ ነበር፡፡

ከዛች ቀን በኋላ የባርሴሎና ቁልፉ ሰው መሆን የቻለው ሊዮ ሜሲ የሶስትዮሽ ዋንጫን ከባርሴሎና ጋር ደጋግሞ ማሳካት የቻለ የክፍለ ዘመኑ የእግር ኳስ ጌጥ ነው፡፡

በርካታ ክብረወሰኖችን የግሉ ያደረገው ሜሲ ስምንት የባሎንዶር ሽልማትን በእጁ ማስገባት የቻለ ሲሆን፥ ይህ ስኬት ከዚህ ቀደም ያልሆነና ወደፊትም የመሆን እድሉ የጠበበ የሜሲ ትንንሽ እግሮች ያስገኙት ፍጹም ከፍታ ነው፡፡

በተጨማሪም ስምንት ጊዜ የፊፋ የአመቱ ምርጡ ተጫዋች መሆን የቻለ እንዲሁም ስድስት የአውሮፓ የወርቅ ጫማ ሽልማትን በማሸነፍ የሚተካከለው የለም፡፡

ሜሲ በአንድ የውድድር አመት 91 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ክብረ ወሰኑን የግሉ ያደረገ ሲሆን፥ ለአንድ ክለብ ማለትም ለባርሴሎና 672 ግቦችን በማስቆጠርም ቀዳሚ ነው፡፡

በላሊጋው 474 ግቦችን በማስቆጠር ብቸኛው ተጫዋች የሆነው የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋች ሊዮ ሜሲ በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች 61 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበልም ተፎካካሪ የለውም፡፡

በ2025 የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ታሪክና ቁጥራዊ መረጃዎች ፌዴሬሽን ሊዮኔል ሜሲን የምንጊዜም የዓለም ምርጡ ተጫዋች ክብርን አጎናጽፎታል፡፡

አይምሬው የግብ አዳኝ፣ ለዐይን ህልም በሚመስሉ የኳስ ምትሃቶቹና በጨዋታ አቀጣጣይነቱ የሚታወቀው ሜሲ እስካሁን 890 ግቦችን ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ከ400 በላይ የግብ እድሎችን ፈጥሯል፡፡

ከባርሴሎና ጋር 10 የላሊጋ፣ አራት የሻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ 34 ዋንጫዎችን በማሳካት አቻ የማይገኝለት ሜሲ የክለቡን የገንዘብ ተግዳሮት ተከትሎ በ2021 ወደ ፒኤስጂ ያደረገው ዝውውር የእግር ኳስ ህይወቱ ብቸኛው የዝቅታ ጊዜ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

በክለብ ደረጃ የተጎናጸፈውን አስደማሚ ስኬት ከሀገሩ ጋር ማሳካት ተስኖት የቆየው አርጀንቲናዊው ኮከብ በ2022ቱ የኳታር ዓለም ዋንጫ ይህንን በማሳካት የተቺዎቹን አፍ አዘግቷል፡፡

አርንጀንቲናን በ2014 የዓለም ዋንጫ እንዲሁም በ2015 ለኮፓ አሜሪካ ፍጻሜ ማድረስ ቢችልም፥ በሁለቱም የፍጻሜ ጨዋታዎች ዋንጫዎቹን ማጣቱን ተከትሎ በርካታ ትችቶችን ማስተናገዱን ተከትሎ በ2016 ራሱን ከብሄራዊ ቡድኑ ማግለሉ ይታወሳል፡፡

ከበርካታ አድናቂዎቹ ጉትጎታ በኋላ ዳግም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ በመመለስ በ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ ሀገሩን የወከለ ሲሆን፥ ከ28 ዓመታት በኋላ በ2021 ከሀገሩ ጋር የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡

በመቀጠልም በ2022 የዓለም ዋንጫን እንዲሁም በ2024 በድጋሚ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን አሳክቷል፡፡

በእግር ኳስ የሚዘጋጁ ሁሉንም አይነት ሽልማቶችን በማሸነፍ ያሸበረቀው ሊዮኔል ሜሲ በ2011፣ 2012 እና 2023 በታይም መጽሄት የዓለም 100 ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችሎም ነበር፡፡

ወደ አሜሪካ በማቅናት ለኢንተር ማያሚ እየተጫወተ የሚገኘው ሊዮ ክለቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሜጀር ሊግ ሶከር ሻምፒዮን እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ በሊጉ በተከታታይ ሁለት ዓመታት የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ያሸነፈ ብቸኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡

ሊዮኔል ሜሲ በአሜሪካ በእግር ኳስ ከፍተኛ ተጽእኖ መፍጠር የቻለ ሲሆን፥ በዚህም በ2023 የታይም መጽሄት የአመቱ ምርጥ ስፖርተኛ በመባል እውቅናን አግኝቷል፡፡

በመላው የእግር ኳስ ቤተሰብ ዘንድ ድንቅ ብቃቱ ስለሚመሰከርለት አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ መንገር ለቀባሪው እንደ ማርዳት የሚቆጠር ነው፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ከተፎካካሪው ፖርቹጋላዊ ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ያለው የአንደኝነት ፍጥጫ እስካሁን የቀጠለ ቢሆንም የ38 ዓመቱ ሊዮ እግር ኳስ ዳግም ሊያያቸው ከማይችላቸው የዘርፉ ተዋንያን መካከል ግንባር ቀደም ነው፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version