Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ቦርዱ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ – ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ አለ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፡፡

ኢዜማ በዛሬው ዕለት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ÷ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በሚያካሂድባቸው አካባቢዎች ሁሉ የሕዝብ ይሁንታን ለማግኘት እሳተፋለሁ ብሏል።

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢዮብ መሳፍንት በዚህ ወቅት ምርጫ የፖሊሲ አማራጮችን ማቅረቢያ፣ የተረጋጋ መንግሥት መመስረቻና የዴሞክራሲ ባህል መገንቢያ መሳሪያ መሆኑን ገልጸው÷ ምርጫውን ለዚህ ዓላማ ብቻ ለመጠቀም እንደሚሳተፍ ጠቁመዋል።

ፓርቲው ላለፉት አራት ዓመታት በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብን ድምጽ ለማግኘት የዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንና በቀጣይ 7 ወራት ውጤቱ የሚታይበት እንደሆነ አመልክተዋል።

የኢዜማ ፓርቲ ሊቀመንበር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ፓርቲያቸው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መንግሥት ለመሆን እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲው መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻዎች ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።

መንግሥት ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አንስተው÷ ገዥው ፓርቲ የሕዝብ ሃብትን ለምርጫ መቀስቀሻነት እንዳይጠቀም እንዲሁም በክርክርና ውይይት መድረኮች እንዲሳተፍ ጠይቋል።

መራጩ ሕዝብ ሃሳብን አመዛዝኖ እንዲመርጥ፣ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን አማራጭ አድርጎ እንዲመርጥ እና ዝግጅት እንዲያደርግ ፓርቲው በመግለጫው ላይ አስገንዝቧል፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከስሜት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ ታቅበው የመፍትሄ ሃሳብ በማቅረብ ምርጫውን ለምርጫ ዓላማ ብቻ እንዲጠቀሙም ነው የገለጸው።

ኢዜማ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ እንዲያተኩርና ባለፈው ምርጫ የታየውን የሎጂስቲክስ እጥረት ቀድሞ መፍታት እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

በመራኦል ከድር

ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
YouTube www.youtube.com/@fanamediacorporation
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Facebook www.facebook.com/wmccwaltamediaandcommunicationcorporate
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
TikTok www.tiktok.com/@fana_television
WhatsApp www.whatsapp.com/channel/0029VbB0dRxG8l59MUkoWR29
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
TikTok www.tiktok.com/@fanamc_entertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

Exit mobile version