አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአምበልነት ምልክት በክንዱ ላይ ያላሰረው የአርሰናሉ መሪ ዴክላን ራይስ የተወለደው በፈረንጆቹ 1999 በለንደን ነው፡፡
ዴክላን ራይስ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በ2006 የቼልሲ አካዳሚን በመቀላቀል ቢሆንም ክህሎቱን የተጠራጠሩት ሰማያዊዎቹ በ14 አመቱ ለዌስትሃም አሳልፈው ሰጥተውታል፡፡
በዌስትሃም ዩናይትድ ራሱን በሚገባ በማጎልበት በተለይ ከ2017 ጀምሮ የመዶሻዎቹ ቁልፉ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡
በመቀጠልም በ2022 የዌስትሃም ዩናይትድ አንጋፋ ተጫዋች የሆነው ማርክ ኖብል ከክለቡ መለያየትን ተከትሎ ራይስ የክለቡ አምበል መሆን ቻለ፡፡
በቀጣዩ ዓመት መዶሻዎቹ የአውሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ ዋንጫን ሲያሸንፉ ራይስ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች በመባል ተሸልሟል፡፡
ለለንደኑ ክለብ 245 ጨዋታዎችን ያደረገው ዴክላን ራይስ በ2023 ወደ ሌላኛው የሰሜን ለንደን ክለብ አርሰናል በ100 ሚሊየን ፓውንድ ተዘዋወረ፡፡
ይህም ዝውውር ከእንግሊዝ የምንጊዜም ወድ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ አካቶታል፡፡
በወቅቱ ሪያል ማድሪድና ማንቼስተር ሲቲን የመሳሳሉ ሃያል ክለቦች ተጫዋቹን ለማዘዋወር ፍላጎት አሳይተው የነበረ ቢሆንም ራይስ የሚኬል አርቴታውን ቡድን ምርጫው አድርጓል፡፡
ወደ መድፈኞቹ ከተዘዋወረ ጊዜ ጀምሮ የወጣበት ውድ የዝውውር ዋጋ ሳይጫነው ወጥ ብቃትን እያሳየ የሚገኘው ራይስ በአርሰናል ቤት የመሪነት ስብዕናን ከተላበሱ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡
በተለይ በሁለገብነቱ፣ ኳስ ይዞ በመቆየት ብቃቱና አስደናቂ በሸርተቴ ኳስ በሚነጥቅበት ችሎታው የሚታወቀውና በሜዳ ውስጥ ድካም የማይታይበት ራይስ በመሪነት ክህሎቱም ሙገሳን እያገኘ ይገኛል፡፡
የ26 አመቱ እንግሊዛዊ ምንም እንኳን በአሰልጣኙ የአምበልነት ሹመትን ባያገኝም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የቡድን ጓደኞቹን በመምራት፣ ትዕዛዝ በመስጠትና ተነሳሽነትን በመፍጠር የሚስተካከለው የለም፡፡
አርሰናል የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ከፍተኛ ጫና ባለበት በዚህ የውድድር አመት ዴክላን ራይስን የቡድኑ ዋና አምበል ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በርካቶች እያነሱ ይገኛሉ፡፡
በዚህም የቀድሞ የመድፈኞቹ አምበልና አንጋፋ ተጫዋች ቶኒ አዳምስ እንዲሁም እውቁ ጋዜጠኛና የአርሰናል ቀንደኛ ደጋፊ ፒርስ ሞርጋን ክለቡ የሊጉን ዋንጫ የግሉ ለማድረግ ራይስን የቡድኑ አምበል ማድረግ አለበት ሲሉ ምክር ሃሳባቸውን በማጋራት ላይ ይገኛሉ፡፡
የቡድኑ አምበል ማርቲን ኦዲጋርድ ባለው የመሪነት ብቃቱ የሚጠራጠሩት ደጋፊዎች በሱ አምበልነት አርሰናል ዋንጫን ማሳካት አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡
ለቡድኑ ያለውን ሁሉንም ነገር ከመስጠቱም ባሻገር ቡድኑ ውጤት በሚያጣበትና ግቦች በሚቆጠሩበት ወቅት ከፍተኛ ቁጭቱንና ብስጭቱን የሚያሳየው ዴክላን ራይስ አርሰናልን ለዋንጫ የሚያንደረድረው ሁነኛ አምበላችን እሱ ነው በማለት ደጋፊዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡
በሊጉ 16ኛ ሳምንት ጨዋታ አርሰናል ወልቭስን 2 ለ 1 ባሸነፈበት ጨዋታ በቡድኑ ብቃት በከፍተኛ ሁኔታ ብስጭቱን ሲገልጽ የታየው ራይስ ቡድኑ የሚያስፈልገው አይነት የመሪነት ባህሪን መላበሱን በርካቶች ሲያነሱ ተስተውሏል፡፡
አያቶቹ የአየርላንድ ተወላጆች የሆኑት ዴክላን ራይስ ለእንግሊዝ መጫወትን ምርጫው ያደረገ ሲሆን በ2019 የመጀመሪያ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን አድርጓል፡፡
ከዛ ጊዜ ወዲህ በ2020 እና 2024 የአውሮፓ ዋንጫ እንዲሁም በ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ሀገሩ እንግሊዝን በመወከል ተጫውቷል፡፡
በበጎ አድራጎት ስራዎቹም የሚደነቀው ራስ አምስት ሚሊየን ዩሮ በማውጣት ለቤት አልባ የሀገሬው ዜጎች ቤቶች መገንባቱም ተነግሯል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓለም ላይ ካሉ ሁለገብ አማካይ ተጫዋቾች መካከል ምርጡ መሆኑ የሚነገርለት ራይስ አርሰናል ለሊጉ አሸናፊነት እያደረገ ላለው ተጋድሎ የአምበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡
በአቤል ነዋይ

