አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በመስቀል አደባባይ እየተገነባ ያለውን የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ አስፈላጊው ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ እድገቷን በማፋጠን በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ስላላቸው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግም ጨምረው ገልፀዋል ፡፡
በቀጣይነትም የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር እና የመስቀል አደባባይ እስካሁን የደረሱበትን አፈፃፀም ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን በጉብኝቱ ላይ የተለያዩ የሀይማኖት መሪዎች መገኘታቸውን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

