Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምና መፍትሄዎቹ…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከባህል፣ ከእሴትና ሥነምግባር ያፈነገጠ ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል አሉ ምሁራን።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው ምሁራን ከባህልና እሴት ያፈነገጡ ይዘቶችን የሚያጋሩ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች መበራከት አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ ሶሺዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ነጋ ጂባት (ዶ/ር) እንደሚሉት፥ ጥቂት የማይባሉ በርካታ ተከታዮችን ማፍራት የቻሉ ይዘት ፈጣሪዎች አፈንጋጭ የሆኑ ይዘቶችን በማጋራት በትውልድ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፡፡

አሉታዊ ይዘቶች ህብረተሰቡ ላይ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ገልጸው፥ ለትውልድ መልካም አርዓያ ስላልሆኑ እልባት ሊበጅላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በጅማ ዩኒቨርስቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው የዲጂታል አለም መስፋት የሚበረታታ ቢሆንም፥ ይዘት ፈጣሪዎች በህጋዊና በተጠየቅ መልኩ እሴትን አክብረው ማገልገል አለባቸው ብለዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ቢሆኑ በተቀደደው ቦይ ከመፍሰስ ይልቅ በዘርፉ እርምት እንዲወሰድ የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመው፥ የሚዲያን አጠቃቀም ከስር ጀምሮ ማስተማር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በወርቅአፈራው ያለው

Exit mobile version