Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮት ዲቯር የሰላም አምባሳደር የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከአፍሪካ የምንጊዜም ምርጥ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የቀድሞው የቼልሲ ኮከብ ዲዲየር ቬስ ድሮግባ የተወለደው በፈረንጆቹ 1978 በኮትዲቯር አቢጃን ነው፡፡

ከአብዛኞቹ ስኬታማ ተጫዋቾች በተቃራኒ ፕሮፌሽናል እግር ኳስን ዘግየት ብሎ የጀመረው አይቮሪያኑ ዲዲየር ድሮግባ በ21 አመቱ ነበር ለፈረንሳዩ የ2ኛ ሊግ ክለብ ሌ ማንስ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው፡፡

በ2003 ወደ ሌላኛው የፈረንሳይ ክለብ ኦሎምፒክ ማርሴይ ዝውውሩን ያደረገ ሲሆን፥ በውድድር አመቱ 19 ግቦችን በማስቆጠር የሊግ-1 ሦስተኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል፡፡

በ2004 ወደ ፕሪሚየር ሊግ በመምጣት የምዕራብ ለንደኑን ክለብ ቼልሲ የተቀላቀለበት 24 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ ወዱ ኮትዲቯራዊ እንዲሆን አስችሎት ነበር፡፡

ቼልሲን በተቀላቀለበት አመት ቡድኑ ከ50 ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ እንዲያሸንፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ሲሆን፥ በቀጣይ የውድድር አመትም በተመሳሳይ ሰማያዊዎቹ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ሲያሳኩ የክለቡ ቁልፍ ተጫዋች ነበር፡፡

በፕሪሚየር ሊግ 100 ግቦችን ያስቆጠረ ቀዳሚው አፍሪካዊ ተጫዋች መሆን የቻለበትን ግብ ያስቆጠረው ደግሞ በ2011/12 የውድድር ዓመት ነበር፡፡

በዚያው ዓመት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቼልሲ ባየርን ሙኒክን በመለያ ምት በማሸነፍ ዋንጫውን ከፍ ሲያደርግ የአቻነቷን ግብ እንዲሁም የማሸነፊያ መለያ ምቷን በማስቆጠር የምሽቱ ጀግና እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

በአስገራሚ ሩጫዎቹ፣ በአየር ላይ ኳስ ብቃቱና በጉልበተኛነቱ የሚታወቀው ድሮግባ የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን በ2006 እና 2009 አሸንፏል፡፡

የቼልሲ የምንጊዜም 4ኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን አብዛኞቹን ስኬታማ ዓመታት ባሳለፈበት ስታምፎርድ ብሪጅ ከእንግሊዛውያን ተጫዋቾች ውጪ ለክለቡ ከፍተኛ ግብ ያስቆጠረ ቀዳሚው ተጫዋች ነው፡፡

ከቼልሲ በተጨማሪ ለቱርኩ ጋላታሳራይ፣ ከቻይናው ሻንጋይ ሽንዋ፣ ለካናዳው ሞንትሪያል ኢምፓክት እንዲሁም ለአሜሪካው ፎኒክስ ራይዚንግ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡

በ2002 ለሀገሩ ኮት ዲቯር መጫወት የጀመረው ዲዲየር ድሮግባ በ105 ጨዋታዎች 65 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የብሔራዊ ቡድኑ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው፡፡

በዚህም ለሀገሩ ኮት ዲቯር ያስቆጠራቸውን 65 ግቦች ጨምሮ በአጠቃላይ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወቱ 367 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድናቸው ብዙ ግቦችን ካስቆጠሩ አፍሪካውያን ተጫዋቾች መካከል 4ኛው ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሲሆን፥ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ቀዳሚው ነው፡፡

ጀርመን ባሰናዳችው የ2006 ዓለም ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎዋን ስታደርግ ሀገሩን በአምበልነት የመራው ድሮግባ በ2006 እና 2012 የአፍሪካ ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችሏል፤ ምንም እንኳን ኮትዲቯር በሁለቱም የፍጻሜ ጨዋታዎች በመለያ ምት ብትሸነፍም፡፡

ድሮግባ በ2010 የደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በ2014 የብራዚል ዓለም ዋንጫዎች ኮትዲቯርን በአምበልነት መርቷል፡፡

በ2006 ኮትዲቯር ሱዳንን በማሸነፍ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ባረጋገጠችበት ወቅት ድሮግባ ካሜራ ፊት በመቅረብ በወቅቱ በሀገሩ ኮትዲቯር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ለነበሩ ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ጥሪ ያቀረበበት አጋጣሚ ልዩ መለያው ተደርጎ ይነሳል፡፡

በጊዜው በሃይማኖት እንዲሁም በፖለቲካ ልዩነት ተቧድነው አደገኛ ግጭት ውስጥ የነበሩ ኃይሎች የእግር ኳሱ ንጉስ ውድ ልጃቸው ያደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እርቅ ማውረዳቸው ይታወሳል፡፡

የዝሆኖቹ አምበል ተናገረ፥ ሀገሩም ጥሪውን ሰምታ አስከፊው የእርስ በርስ ግጭት አብቅቶ ድሮግባም ሀገሩም አሸናፊ ሆነዋል፡፡

በስፖርቱ የነበረውን ተሰሚነት ለሀገርና ለህዝብ በማዋል ለሌሎች አርዓያ የሆነበትን የተግባር ትምህርትን የሰጠው የቼልሲ ብሎም የኮትዲቯር የሜዳና ከሜዳ ውጪ ጀግና በፈረንጆቹ 2018 ከነገሰበት እግር ኳስ በክብር ተሰናበተ፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version