Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የዓሣ ኃብት ልማት ሽፋንን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል እንሰሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ቢሮ በክልሉ የዓሣ ኃብት ልማት ሽፋንን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አለ።

በቢሮው የዓሣ ቴክኖሎጂ ባለሙያ አበበ ፋንታሁን እንዳሉት፤ ክልሉ ለዓሣ ኃብት ልማት ምቹ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃ መገኛ ነው።

አሁን ላይ በክልሉ ዓመታዊ የዓሣ ምርት ከ40 ሺህ ቶን በላይ መድረሱን ገልጸው፤ እስካሁን ለዓሳ ምርት ያልዋሉ የውሃ መገኛዎችን ለማልማት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት በአዳዲስ የውሀ መገኛዎች ላይ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የዓሣ ጫጩቶች ለማሰራጨት ታቅዶ በ5 ወራት ውስጥ 600 ሺህ በላይ ጫጩቶችን ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።

በደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 3 ግድቦች ላይ ዓሣ ለማርባት ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ለአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ የዓሣ ጫጩቶች ወደ ግድቦቹ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለዓሣ እርባታ ተስማሚ የሆኑ 30 ወረዳዎች ተለይተው አርሶ አደሮች ዓሣ እንዲያረቡ የሚያስችሉ ከ400 በላይ ኩሬዎች ተዘጋጅተው የጫጩት ስርጭት እየተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር እንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ታሪኳ እሸቱ፤ በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ 3 ግድቦች ላይ ዓሣ ለማርባት የሚያስችል ስራ ተጀምሯል ብለዋል።

ዘርፉን በማስፋት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር የስራ ዕድል መፍጠሪያ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተደራጁ ወጣቶችን ለማብቃት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በግርማ ነሲቡ

Exit mobile version