አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ተቋማት የሰላም አካቶ ትግበራን በዕቅዳቸው አካትተው ሊተገብሩ ይገባል አሉ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የፌደራልና የክልል ምክር ቤቶች በህግ ማውጣት፣ በክትትልና በቁጥጥር ሥራዎቻቸው የሰላም አካቶ ትግበራን እውን ማድረግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።
የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ከቀበሌ እስከ ፌደራል ያሉ የመንግስት መዋቅሮች አገልግሎት ሲሰጡ የህዝብን ፍላጎትና ተጠቃሚነት መሰረት ማድረግ አለባቸው፡፡
ሰላም በአንድ ተቋም ብቻ የሚመጣ ሳይሆን በሁሉም ግለሰቦች፣ ተቋማትና አደረጃጀቶች ውስጥ ያለ አንኳር ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፥ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር ባለ መስተጋብር የሚገኝ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ሰላም የሚጀምረው እያንዳንዱ ተቋም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሲችል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የዚህ ድምር ውጤት የሀገርን ሰላም እንደሚያረጋግጥ አስረድተዋል።
ተቋማቱ ሰላምና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በዕቅዳቸው ማካተት፣ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች ሰላምን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ማድረግና አገልግሎት አሰጣጥን ለሰላም ግንባታ በሚያግዝ መልኩ መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

