Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

4ኛው ኢንቨስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 4ኛው ኢንቨስት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ከመጋቢት 17 እስከ 18/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በፎረሙ ከ7 መቶ በላይ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና አጋር የልማት ድርጅቶች የሚሳተፉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላትን ዝግጁነት የምታሳይበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢንቨስትመንት ቁልፍ ዘርፎች የሆኑት ግብርና፣ አይሲቲ፣ ማዕድን፣ ታዳሽ ኃይል እና ቱሪዝም በፎረሙ በስፋት እንደሚተዋወቁ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

በተጨማሪም በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል የፖሊሲና የኢንቨስትመንት ውይይት፣ የአቻ ለአቻ ቢዝነስ ውይይቶች፣ አውደ ርዕይ እንዲሁም በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የጉብኝት መርሐ ግብሮች በፎረሙ ተካትተዋል፡፡

በፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማዘመን እየተገበረች ያለውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያና አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ አዲስና የማስፋፊያ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩ ተመላክቷል፡፡

ፎረሙ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገንዘብ ሚንስቴርና የልማት አጋር ድርጅቶች በትብብር እንደሚዘጋጅ ነው የተገለጸው፡፡

Exit mobile version