Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ወሳኝ የሆነው የማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም …

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል አሉ የዘርፉ ባለሙያዎች።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች አማካሪ ቴዎድሮስ ደርበው እንዳሉት÷ የማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ጎብኚዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እንዲቀራረቡና ረዘም ያለ ቆይታ እንዲኖራቸው ያግዛል።

ይህም ጎብኚዎች የማሕበረሰቡን ባህል፣ እሴት፣ ማንነትና የአኗናር ዘዬ በሚገባ እንዲረዱ በማድረግ አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በመዳረሻ ልማት ሥራዎችና የቱሪዝም ዘርፍን በማሳደግ ሒደት ውስጥ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ጎብኚዎችን የሚይዙና የሚያሳትፉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጎብኚዎች በሚሄዱባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ማሕበረሰቦች ጋር በመቀራረብ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ የሚያደርጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ የተለያዩ ዓይነት የቱሪዝም ሥራዎቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡና ኢትዮጵያም ለየትኛውም ዓይነት የቱሪዝም ሥራ ምቹ የሆነ ሥነ ምሕዳር እንዳላት አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ እምቅ ሃብት ያላት ኢትዮጵያ መጠቀም የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ለቱሪዝም ሥራው ምቹ የሆነ ሥነ ምሕዳር ብቻውን ተወዳዳሪ ለመሆን በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰው÷ እነዚህን ሃብቶች በመሰረተ ልማትና ሌሎች ሥራዎች ማስፋፋትና ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

የባሕል እና ቱሪዝም ጋዜጠኛ የሆኑት ዘሪሁን ግርማ በበኩላቸው ማሕበረሰብን መሰረት ያደረገ ቱሪዝም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ ለዚህ ዓይነት የቱሪዝም ሥራ ምቹ መሆኗን አስረድተዋል።

የማሕበረሰብ ባሕል፣ ወግና ትውፊት ከተፈጥሮ ጋር ሲተሳሰሩ ማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝምን መፍጠር እንደሚያስችል ነው ያብራሩት፡፡

 

በተለያየ መልኩ ቱሪስቶች ሊጎበኙ የመጡትን ባሕል እና ልማድ መሞከር እና መለማመድ እንደሚፈልጉ አንስተዋል።

በመሆኑም የማሕበረሰቡን ባሕል እና ወግ ባከበረ መልኩ አብረው እንዲያሳልፉ እንዲሁም የአካባቢውን ባሕል እንዲጋሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የማሕበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ሥራ በተለይም ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ከፍተኛ ጥቅም ያለው በመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

 

Exit mobile version