አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ የእቅድ ግብዓቶች መካከል አንዱ ዲጂታል የወሳኝ ኩነት እና የነዋሪነት አገልግሎት ስርዓት ነው፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) አገልግሎቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፥ ስርዓቱ በሀገር በቀል ተቋምና በሀገር በቀል ባለሙያዎች በጥራት የለማ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሰርዓቱ በወረዳ፣ በዞን፣ በከተሞችና በክልሎች አንድ አይነት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፥ ይህም የወሳኝ ኩነትና የነዋሪነት አገልግሎት እንዲቀላጠፍና ወጥ እንዲሆን ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ዲጂታል ስርዓቱ የወሳኝ ኩነት፣ የቤተሰብ ምዝገባ፣ የነዋሪነትና ዜግነት፣ የዝምድና ማረጋገጫና ሌሎች አገልግሎቶችን በወጥነት ለመስጠት ያስችላል፡፡
በተጨማሪም የወሳኝ ኩነትና የነዋሪነት አገልግሎት ሰነዶች ትክክለኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችል ስርዓትን ያካተተ ሲሆን፥ ዜጎች ባሉበት ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡
ስርዓቱ በሞባይል መተግበሪያ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ዜጎች በወሳኝ ኩነት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በቀጥታ እንዲያቀርቡ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ

