አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ አስተሳሳሪ የሆነ የጋራ ትርክት ያስፈልጋል አሉ።
አቶ አደም ፋራህ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ከተወሰዱ ወሳኝ እርምጃዎች ውስጥ የኢትዮጵያን አስተሳሳሪ ትርክት በመለየት መቅረጽ ነው።
ብሔራዊነት የኢትዮጵያ አስተሳሳሪ ትርክት መሆኑን ገልጸው፤ ይህም በነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሃዊነት፣ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ ትናንት፣ ዛሬና ነገን የሚያስተሳስር ገዢ ትርክት እንደሆነ አስረድተዋል።
የብሔራዊነት ትርክት ያለፈውን በአግባቡ መዝኖ ያሉ መልካም ነገሮችን ለማስቀጠል፣ የነበሩ ህጸጾችን ለማረም እንዲሁም የወደፊቱን ተስፋ ለማለምለም እና ስጋቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
ትርክቱ የጋራ ማንነትን እና ሀገርን በሁሉም ከሁሉም ለሁሉም ለመገንባት የሚያገለግል መሆኑን አብራርተዋል።
የተቀረጸውን ትርክት የማስረጽ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ብልጽግና ፓርቲ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአመራርና አባላቶች ደረጃ በጉዳዩ ላይ በመምከር መግባባት ተፈጥሯል ያሉት አቶ አደም ፋራህ፤ የብሔራዊነት ትርክትን ለማስረጽ በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝና ለውጦች እንደመጡ ጠቁመዋል።
የብሔራዊነት ትርክቱ ገዢ እንዲሆን ተቋማት ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ተግባር የብሔራዊነት ትርክት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ኖሮ ማሳየት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከትርክቱ ጋር የተቃረኑ ድርጊቶች ዋጋ ሊያስከፍሉ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ከፋፋይ የሆኑ ነጠላ ትርክቶችን በመታገል የብሔራዊነት ትርክትን ማስረጽ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ

