Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባኔ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ማሮ” በዓል እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የባኔ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ማሮ” በዓል እየተከበረ ነው።
የባኔ ብሔረሰብ አባላት በየዓመቱ ታኅሳስ 15 ቀን አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ዓመት ይቀበላሉ።
የብሔረሰቡ አባላት የዘመን መለወጫ በዓላቸውን ዛሬ በደቡብ ኦሞ ዞን ቀይ አፈር ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እና በፓናል ውይይት አክብረዋል።
በዓሉ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የብሔረሰቡ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዓሉ አብሮነት፣ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ጠቃሚ እሴቶች መያዙ የተገለጸ ሲሆን፤ በዓሉ ጎልቶ እንዲተዋወቅ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
ትውልድ በማነፅ፣ አብሮትንን በማጠናከር፣ ሰላምን በማፅናትና እርስ በርስ በመደጋገፍ በኩል በዓሉ ጠቃሚ ሚና እንዳለው ተነግሯል።
የበዓሉ እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ እንደሚሰራ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
የባኔ ብሔረሰብ የራሱ የሆነ የቀን፣ የሣምንታት፣ የወራትና የወቅቶች አቆጣጠር ቀመር ያለው ሲሆን፤ የብሔረሰቡ አባላት በየዓመቱ ታኅሳስ 15 ቀን አሮጌውን ዓመት ሸኝተው አዲሱን ይቀበላሉ።
በዓሉ የበደለ የሚክስበት፣ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተቸገሩ የሚጠየቁበትና አብሮነት የሚጎላበት መሆኑን የደቡብ ኦሞ ዞን ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
Exit mobile version