Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል በ6 ሺህ 386 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ይከናወናል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ3 ነጥብ 193 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተጠናቅቋል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡

በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብሩ እንዳሉት ÷ የአካባቢ ሥነ ምሕዳርን መጠበቅ የሚያስችለውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በስኬት ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በተለይም ሕብረተሰቡ በዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ በንቃት እንዲሳተፍ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

3 ነጥብ 193 ሚሊየን ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመው ÷ በዚህም 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል፡፡

ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚውሉ የቁፋሮና ሌሎች መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው እንዲሳለጥ ለግብርና ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የሚከናወንባቸው 6 ሺህ 386 ተፋሰሶች ተለይተዋል ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፡፡

በመጪው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ይፋ በሚደረገው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

Exit mobile version