አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዳሽን ባንክ አ.ማ ባለአክሲዮኖች 32ኛ መደበኛ እና 28ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
የዳሸን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ባንኩ በተጠናቀቀው 2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ የፋይናንስ አፈጻጸም በማስመዝገብ አጠቃላይ ገቢውን 31 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አድርሷል፡፡
ገቢው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ34 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸው÷ ይህ ከፍተኛ ገቢ የባንኩን ውጤታማ የአሠራር ስልቶችና ፈታኝ በሆነው የኢኮኖሚ ሥነ ምህዳር ውስጥ ያለውን ጠንካራ አቅም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ ሃብቱን ከ254 ቢሊየን ብር በላይ ያሻገረ ሲሆን÷ ይህም በቀደመው የበጀት ዓመት ከነበረው 183 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጋር ሲነፃፀር የ38 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
የዳሸን ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 202 ነጥበብ 2 ቢሊየን ብር መድረሱን የተናገሩት አቶ ዱላ መኮንን ÷ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ38 ነጥብ 7 በመቶ ጉልህ ጭማሪ ማሳየጡን ጠቅሰዋል፡፡
ከጠቅላላው የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ የዳሸን ባንክ ወለድ ነፃ አገልግሎት (ሸሪክ) የ15 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር አስተዋጽኦ አድርጓልም ነው ያሉት፡፡
ባንኩ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ረገድ ከፍተኛ አፈፃፀም ያስመዘገበ ሲሆን÷ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ15 ነጥብ 58 በመቶ ጭማሪ ያለው 1 ነጥብ 12 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቱ ተመላክቷል፡፡
ዳሸን ባንክ በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር አጠቃላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ጠቅሰው ÷ ትርፉ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 1 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል፡፡
የወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ጨምሮ የባንኩ አጠቃላይ የብድር ክምችት መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ 134 ቢሊዮን ብር መደረሱ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል የባንኩ ካፒታል ባለፈው የበጀት ዓመት መጨረሻ የ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ዕድገት በማሳየት 14 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ደርሷል።
ዳሸን ባንክ በኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ መሪነቱን ያስመሰከረበትን የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለባንክ ኢንዱስትሪው እንዳበረከተም ተገልጿል፡፡
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው÷ በበጀት ዓመቱ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ላሳዩት ያልተቋረጠ ድጋፍ፣ ደንበኞች ለጣሉት እምነት እንዲሁም የባንኩ ሰራተኞች የላቀ አገልግሎት በመስጠት ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዳሸን ባንከ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር 7 ነጥብ 88 ሚሊየን እና የቅርንጫፎቹን ቁጥር ደግሞ በዓመቱ መጨረሻ 906 መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ባንኩ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራትን ከመወጣት ረገድ ለማህበረሰብ ተኮር ስራዎች እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሞች 108 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ፈሰስ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

