Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ ለሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የሀይማኖት ተቋማት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀይማኖት ተቋማት በመዲናዋ እየተከናወኑ ለሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ይመር ከበደ።

ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ማህበራዊ ኃላፊነት ደንብ ዙሪያ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ይመር ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የለውጡ መንግስት በከተማዋ የነበሩ የተደራረቡ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመመርመር በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል።

የከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው የሚገኙ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሀይማኖት ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሕብረተሰቡን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታትና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በትብብርና በመረዳዳት ለመሻገር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር የሀይማኖት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው፥ በልማት፣ በሰላም፣ ትውልድን በማነፅና በሀገር ግንባታ የሀይማኖት ተቋማት ከመንግስት ጎን ተሰልፈው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የአዲስ አበባ የኃይማት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የኃይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

በገብረማርያም ወ/ገሪማ

Exit mobile version