አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጨቅላ ሕፃናትና የእናቶች ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማጠናክር የሚውል በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ 206 የጤና ተቋማት የኮምፒውተር ድጋፍ ተደርጓል፡፡
የጨቅላ ሕጻናትን ሞት ከመቀነስና የእናቶችን ጤና ከማሻሻል ረገድ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም የመረጃ አያያዝን ከማዘመንና ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ከማድረግ ረገድ አሁንም በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ ተመላክቷል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ሳህረላ አብዱላሂ ለሆስፒታሎቹ የተደረገው ድጋፍ የመረጃ አያያዙንና የሪፖርት ስርዓቱን በየደረጃው በማዘመን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለውሳኔ ሰጪዎች ወቅታዊ እና ታዓማኒነት ያለው መረጃ ማድረስ ያስችላል ብለዋል፡፡
ከጤና አገልግሎት ጥራትና ቀልጣፋነት አንፃር ከንድፈ ኃሳብ ባለፈ ተቋማት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት እና ተግዳሮቶችን በመለየት መደገፍ የፕሮጀክቱ አንዱ አላማ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኤስኤልኤል ፕሮግራም ኃላፊ አቶ አብይ ሰይፉ ናቸው፡፡
ከእዚህ በተጨማሪ መጠነኛ የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ስልጠናዎች ለተመረጡ ተቋማት እየተሰጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በአጠቃላይ 412 ዴስክቶፕ ኮምፒውተሮችን ለተመረጡ 206 ሆስፒታሎች በመደገፍ የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ አያያዝን ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል ጤና ሥርዓትን ለማጠናከር የሚውሉ ሲሆኑ÷ የየሆስፒታሉ እና የየክልሉ ጤና ቢሮ ተወካዮች በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል።

