አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለጂሰስ ፕሮፌቲክ ስፕሪት ቸርች (ጄፒኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ) ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጯቸው ይዘቶችን አስመልክቶ ባለሥልጣኑ ባወጣው መግለጫ፤ በሀገራችን የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መረጋገጡ ይታወቃል ብሏል።
በዚሁ መሰረት በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 መሰረት የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ምዕመኖቻቸው ባሉበት ሆነው በመገናኛ ብዙኃን አስተምህሮቶቻቸውን እንዲከታተሉ ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልጿል።
ባለሰልጣኑ መገናኛ ብዙኃን ተግባሮቻቸውን ህግና ሙያዊ ስነ ምግባርን በማክበር ስለማከናወናቸው ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ክፍተቶች እንዲታረሙ ግብረ መልስ ይሰጣል፣ እንደ ጥፋቶች ዓይነትም ተገቢውን አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ጄፒኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ ታህሣሥ 13 ቀን 2018 ዓ.ም በማህበራዊ ገጾቹ ላይ ያሰራጨውን ፕሮግራም ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/13 እና አግባብነት ካላቸው ህጎች አንጻር የክትትል ስራዎችን አከናውኗል፡፡
ፕሮግራሙ በሀገራችን የሰላሌ አካባቢን ተገቢ ባልሆነ መልኩ መገለጹን ማረጋገጥ ተችሏል ያለው ባለስልጣኑ፤ በዚህም መሰረት ለጄፒኤሰ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የተጠቀሱ የህግ ድንጋጌዎችን በመጣሱ ማሰጠንቀቂያ ተሰጥቶታል ብሏል።
በቀጣይም ከላይ የተጠቀሱትን ህጎች ጥሰው የተገኙ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ገልጾ፤ መገናኛ ብዙኃን ያሉባቸውን ሃላፊነቶች ተገንዝበው በጥንቃቄና በሃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩ አሳስቧል።

