Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በፖሊሲ የተደገፈ መፍትሔ የሚሹት የዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች…

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩኒቨርሲቲዎች የማስተማሪያ ሆስፒታሎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በፖሊሲ የተደገፈ መፍትሔ ያስፈልጋል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ።

ለጅማ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ማዕከል 25 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርጓል።

ሚኒስትር ዴኤታው በድጋፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት፥ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ከማስተማር ባሻገር የጤና አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ሆስፒታሎቹ የባለቤትነት፣ የአስተዳዳርና የፋይናንስ ችግሮች እንዳሉባቸው ጠቅሰው፥ ችግሮቹን ለመቅረፍ የትምህርት ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው ብለዋል።

የህክምና ፋይናንስ ስርዓት የጤና ልዩ ባህሪን ያገናዘበ እንዳልሆነ ገልጸው፥ ለጤናው ዘርፍ በቂ በጀት መመደብ ካልተቻለ የማስተማሪያ ሆስፒታሎችን ችግር ለመቅረፍ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

ይህንን የሚመጥን አደረጃጀት ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባፊጣ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ከተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ህክምና ማዕከል የተደረገው የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ጥራት ያለው የተሳለጠ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ ያለውን የህክምና ትምህርትና አገልግሎት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በወርቅአፈራው ያለው

Exit mobile version