አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና-ኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ በቻይና ሁናን ግዛት ጁጆ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ኮንፈረንሱ የኢትዮጵያን ቡና በቻይና ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ከአምስት አመት በፊት ቻይና በኢትዮጵያ ቡና መዳረሻነት ከነበረችበት የ33 ደረጃ ዘንድሮ ወደ አራተኛ ከፍ ማለቷ ተገልጿል፡፡
የቻይና እና ኢትዮጵያ የቡና ኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ኮንፈረንስ ይህን ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ለማሳደግ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በኮንፈረንሱ የጁጆ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቻይና ወዳጅነት ኮሚቴ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በተጨማሪም በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው፣ የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር)፣ የመንግስት ኮሙኑኬሽን አገልገሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እና የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡
በኮንፈረንሱ የኢትዮጵያን ባለ ልዩ ጣዕም ቡና የመቅመስ ፕሮግራም የተዘጋጀ ሲሆን በዚህ ዝግጅት 700 ሺህ ሰው ይሳተፍበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

