Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 ጉምሩክ ኮሚሽን ከመደኛ ስራው በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል – ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተቋሙ ከመደበኛ ስራው በተጨማሪ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል አሉ።

የኮሚሽኑ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ያስገነባውን የሼህ አሊ ጉሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በዛሬው እለት አስመርቋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዳሉት፤ ጉምሩክ ኮሚሽን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም ትውልድን ለመቅረፅ በሚደረገው ርብርብ በትምህርት ዘርፍ ላይ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሼህ አሊ ጉሬ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአብነት አንስተዋል።

በትውልድ ላይ ዘላቂ ለውጥ የሚያመጣ እና ዘመን የሚሻገር ስራ መበረታታት እንዳለበት ገልጸው፤ በተቋሙ የማህበራዊ ኃላፊነት ተግባራት ንቁ ተሳትፎ ለሚያደርጉ ሰራተኞች እና አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል።

የሶማሊ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው፤ ጉምሩክ ኮሚሽን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው፤ ይህ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በክልሉ የኮንትሮባንድ እና ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን የመከላከል ስራ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ጉምሩክ ኮሚሽን ከህብረተሰቡ ጋር ይበልጥ ተቀናጅቶ በመስራቱ የመጣ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በዳዊት ጎሣዬ

Exit mobile version