አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ምሽት ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
አስቶን ቪላ በሁሉም ውድድሮች ያለፉትን 11 ጨዋታዎች ማሸነፉን ተከትሎ በምሽቱ ጨዋታ ለሊጉ መሪ አርሰናል ከባድ ተጋጣሚ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አስቶን ቪላ ሦስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ያለው ሲሆን፥ አርሰናል አንዱን አሸንፎ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል፡፡
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት ከ15 በኢምሬትስ ይደረጋል፡፡
በተመሳሳይ 5 ሰዓት ከ15 ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ ግርጌ የሚገኘውን ወልቭስ በኦልድትራፎርድ ያስተናግዳል፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች በርንሌይ ከኒውካስል፣ ቼልሲ ከቦርንማውዝ፣ ኖቲንግሃም ፎረስት ከኤቨርተን፣ ዌስትሃም ዩናይትድ ከብራይተን ምሽት 4 ሰዓት ከ30 የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

