Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አርሶ አደሮች የጀመሩት ሥራ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያሳይ ነው – አቶ አዲሱ አረጋ

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሕይወታቸውን ለመቀየር የጀመሩት ሥራ የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ መሆኑን የሚያሳይ ነው አሉ፡፡

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ዙሪያና ሸበዲኖ ወረዳዎች በአርሶ አደሮች እየተከናወኑ ያሉ የአትክልት ልማት እንቅስቃሴዎች ጎብኝተዋል፡፡

አቶ አዲሱ አረጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ከዚህ በፊት የእርዳታ እህል ይሰፈርላቸው የነበሩ አርሶ አደሮች በአትክልት ልማት ተሰማርተው በምግብ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው የተሻለ ገቢ እያገኙ ነው።

በክልሉ በአንደኛ ዙር መስኖ 80 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ አትክልቶች መልማቱን ገልጸው፥ 18 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የሲዳማ ክልል አርሶ አደሮች በላባቸው ደማቅ ታሪክ እየፃፉ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በክልሉ ያለውን የሆርቲካልቸር ልማት ለማጠናከር መንግስት አስፈላጊውን ግብዓትና ድጋፍ እንደሚያርግ አረጋግጠዋል፡፡

በክልሉ የሆርቲካልቸር ስራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በበኩላቸው መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት፣ ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም የተፈጠረልን የገበያ ትስስር በሕይወታችን ላይ የሚታይ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የሆርቲካልቸር ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በጥላሁን ይልማ

Exit mobile version