አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜማና ግጥም ደራሲ እንዲሁም ፕሮዲውሰር አርቲስት ያየህይራድ አላምረው መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍት በዛሬው ዕለት ተመርቋል፡፡
አርቲስቱ በሕይወት ዘመኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ መጽሐፍትና ሌሎች የመረጃ ሃብቶችን በማደራጀት ነው የመታሰቢያ ቤተ መጽሐፍቱ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ተመርቆ ክፍት የተደረገው፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ፣ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው እንዲሁም የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አንጋፋ የጥበብ ከያኒዎች ተገኝተዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚህ ወቅት አርቲስት ያየህይራድ ለመጽሐፍት ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን አንስተው÷ የመጽሐፍቱ በዚህ ደረጃ መሰብሰብ የሚደነቅና ለአርቲስቱም ትልቅ ማስታወሻ የሚሆን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰርጸ ፍሬስብሃት በበኩላቸው÷ ያየህይራድ የዘፈን ግጥም ደራሲነት ያለውን ከባድ ፈተና በመሻገር ታላቅ የጥበብ ሰው እንደሆነ ማስመስከሩን አውስተዋል፡፡
አርቲስቱ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ውስጥ ያለው ወመዘክር እና መታሰቢያ ቤተ መጽሐፍት የትውልዶች ሁሉ ማስተማሪያ መሆኑን ተናግረዋል ።
ከያኒ ያየህይራድ አላምረው በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ የጥበብ ሰው ነው።
“ቆሜ ልመርቅሽ” የተሠኘው የጥላሁን ገሰሰ ዘፈን ግጥም ደራሲ ሲሆን÷ የአስቴር አወቀ “ሰበቡ” አልበም ሙሉ ድርሰት ባለቤት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
ለኃይልዬ ታደሰ “ይሞታል ወይ” ሙሉ አልበምን ፕሮዲውስ ከማድረግ ባለፈ “የኢትዮጵያ አምላክ” እና “ይሞታል ወይ” የተሰኙ ሥራዎችም የአርቲስቱ ድርሰቶች ናቸው።
ከድርሰት ሥራዎቹ መካከል ለጽጌሮማን አስናቀ (ባቲ)፣ ለጸጋቸው ሀይለኢየሱስ (ለምለም) እንዲሁም ለታደለ ሮባና ለብርሃኑ ተዘራ የሰራቸው ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡
የቤተ መጽሐፍቱ መከፈት አርቲስቱ በሕይወት ዘመኑ መጽሐፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ጋዜጦችን በማሰባሰብና በማንበብ የጥበብ ሥራ በእውቀትና ንባብ ላይ ተመርኩዞ መሠራት እንደሚገባው ያስመሰከረበትን ተሞክሮ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችላል።
በሶስና አለማየሁ
ፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
Facebook www.facebook.com/fanabroadcasting
Facebook https://web.facebook.com/fanasport
Telegram t.me/fanatelevision
Website www.fanamc.com
Amharic Entertainment YouTube www.youtube.com/@fanaentertainment
Amharic Podcast YouTube www.youtube.com/@fanamcpodcast በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስለሆኑ እናመሰግናለን!

