አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ290 ሺህ 545 ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ግርና ቢሮ፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ም/ ሃላፊና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መላኩ ባፋ እንዳሉት ÷ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአፈር ለምነትና ምርታማነትን ከማሻሻል ባለፈ የአካባቢ ሥነ ምሕዳርን መጠበቅ ያስችላል፡፡
የዘንድሮውን አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በስኬት ለማከናወን አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
በክልሉ በ290 ሺህ 545 ሔክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን እቅድ መያዙን ነው የገለጹት፡፡
ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው 1 ሺህ 294 ተፋሰሶች መለየታቸውን ጠቁመው ÷ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንደሚሳተፉ አቶ መላኩ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ሕብረተሰቡ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው በንቃት እንዲሳተፍ በአደረጃጀት የመለየት፣ የግንዛቤ ፈጠራ፣ የቅየሳና የእርሻ መሣሪያ ዝግጅት መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ለግብርና ባለሙያዎችና ለቀያሽ አርሶ አደሮች ሥልጠና መሰጡን ነው ያስረዱት፡፡
በመጪው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ በይፋ በሚጀመረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ንቅናቄ የክልሉ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ

