Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል ለገና በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመጪው ገና በዓል መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እየቀረቡ ነው አለ የክልሉ ንግድ ቢሮ፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ገሾ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ በበዓሉ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም በክልል ደረጃ አምስት የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
ከመደበኛ ገበያ በተጨማሪ በባዛሮችና ዐውደ ርዕይዎች እንዲሁም በ700 የሰንበት ገበያዎች የበዓል ፍጆታ እቃዎች ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡
ለበዓሉ የተለያዩ የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች በብዛትና በጥራት ለገበያ እንዲቀርቡ ትስስር መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡
ለገና በዓል በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በትስስር ከአስመጪዎችና ፋብሪካዎች ጋር ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር በላይ ዘይት እና ከ250 ሺህ በላይ በግና ፍየል ለገበያ እየቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም 49 ሺህ 960 ኩንታል በቆሎ፣ 18 ሺህ 262 ኩንታል ስንዴ፣ 36 ሺህ 134 ኩንታል ጤፍ፣ 500 ሺህ ቶን በላይ አትክልትና ፍራፍሬ ለገበያ እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም 5 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ዶሮ፣ 22 ሚሊየን እንቁላል፣ በዩኒየኖች በኩል በትስስር የሚቀርብ 21 ሺህ 105 ኩንታል በላይ ስኳር እና 31 ሺህ 666 የስንዴ ዱቄት ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለገና በዓል በቂ ምርት መኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸምት ያስገነዘቡት ም/ሃላፊው÷ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ዜጎች ለበዓሉ ጊዜ ያለፈባቸውንና ባዕድ ነገር የተቀላቀለባቸውን ምርቶች እንዳይገዙ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በክልሉ ሁሉም ደረጃዎች የተዋቀረው ኮሚቴ የበዓል ገበያው በተገቢ ሁኔታ እንዲሳለጥ አስፈላጊውን ቁጥጥር እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት፡፡
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version