Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ነሃሴ 15፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ክረምቱን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ጥንቃቄ ስራ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፀው ለወባ ተጋላጭ በሆኑ 2 ነጥብ 8 ቤቶች የኬሚካል ርጭት ይከናወናል ተብሏል፡፡

አማራ እና ደቡብ ክልል ላይም ስርጭቱ ሊሰፋ ስለሚችል በትኩረት እንደሚሰራበት ጠቅሶ ሚኒስቴሩ ከ 6 ሚሊየን በላይ አጎበር እየተሰራጨ መሆኑንም አስታውቋል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰሎሞን እንደተናገሩት ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት አመት በነበረው የዝናብ ሁኔታ እና መሰል ምክንያቶች የወባ ስርጭት በሀገራችን ከፍ ብሎ ታይቷል።

ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ ያለው የስርጭት መጠን ዝቅ እያለ ቢመጣም ባሳለፍነው አመት ከ1 መቶ በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ ህይወታቸውን ማጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁንም ክረምቱን ተከትሎ የወባ ስርጭት ሊከሰት እንደሚችል የገለፁት ዳይሬክተሯ በተለይም አማራ እና ደቡብ ክልሎች ላይ ሰፊ ስራን እንደሚጠይቅ እና ስርጭቱ ከፍ ሊልባቸው እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

ባሳለፍነው አመትም በአማራ እና ደቡብ ክልል ላይ ስርጭቱ ከፍ ብሎ ታይቶ እንደነበር ታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም ስጋቱ ያለባቸው እና የተለዩ ቦታዎች ላይ የኬሚካል ርጭት ስራ ይከናወናል ተብሏል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ቤቶች የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት የሚከናወንባቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ህብረተሰቡ በጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች የሚሰጡ የመከላከያ መንገዶችን በመተግበር ከወባ በሽታ እራሱን እንዲከላከል ጥሪ ቀርቧል።

ኢትዮጵያን በፈረንጆቹ 2030 ከወባ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

በዙፋን ካሳሁን

Exit mobile version