Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ የምስራች ነው – ሰላማዊት ካሳ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ መጀመር ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ የምስራች ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን አስጀምረዋል፡፡

ሰላማዊት ካሳ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ መጀመሩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ÷ የአየር ትራንስፖርት እና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ ዘርፎች ናቸው፡፡

በዚህም ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመር ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ የምስራች ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በዓመት 60 ሚሊየን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ሲሆን÷ ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከዓለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኸሪያዎች አንዷ ያደርጋታል፡፡

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡

በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሲሆን ÷ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትም ያጠናክራል፡፡

Exit mobile version