Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው የአፍሪካ አቪዬሽን ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ ርምጃ ነው – አቶ መስፍን ጣሰው

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት አስሮ የያዘውን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ ርምጃ ነው አሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው በዚሁ ወቅት÷ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ እጅግ ትልቅና ዘመናዊ እንዲሁም አንድ መለስተኛ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናሎች እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል።

ሁለት በተጓዳኝ የሚሰሩ የአውሮፕላን መንደርደሪያዎች እንዲሁም 180 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚያስችል ቦታ ይገነባልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም 350 ማረፊያ ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ ሆቴል በተርሚናሉ ውስጥ እንደሚገነባ ገልጸው÷ በዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን ጭነት የሚያስተናግድ የካርጎ ተርሚናልና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከልም በዚሁ ምዕራፍ እንደሚገነባ አስታውቀዋል።

አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ከነባሩ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር በፈጣን ባቡር እና በፈጣን የመኪና መንገድ እንደሚገናኝ አስረድተዋል።

ይህ ግዙፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የአፍሪካን አቪዬሽን እድገት አስሮ የያዘውን የመሰረተ ልማት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተወሰደ ትልቅ ርምጃ እንደሆነም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ አሕጉርም ትልቅ አርአያ እንደሚሆን ተናግረው÷ በተለይም የአፍሪካ ነፃ አሕጉራዊ ንግድ ቀጣናን ተግባራዊነት ለማቀላጠፍና የአሕጉሪቱን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር ለማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አውሮፕላን ማረፊያው ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው÷ ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ የሚመሰረተው የኤርፖርት ከተማም በንግድ፣ በኢንዱስትሪና በቱሪዝም ዘርፎች ለአካባቢው ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

Exit mobile version