አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ በባሌ ዞን በሮቤ እና በጎባ ከተሞች ጉብኝት አደረገ፡፡
ልዑኩ በባሌ ዞን በሮቤ እና በጎባ ከተሞች ውድመት ደርሶባቸው በህዝብ ተሳትፎ እየተገነቡ ያሉ ሆቴሎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም በሮቤ ከተማ እየተገነባ ያለውን 30 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ እና 187 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ መናኸሪያ፣ 10 ሄክታር ቦታ ላይ ያረፈና 773 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሮቤል ኢንዱስትሪያል ፓርክ እንዲሁም 148 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸውን በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ አራት ትምህርት ቤቶችን ጎብኝቷል።
በዞኑ 2 ሆቴሎች፣ 80 የመኖሪያ ቤቶች እና 46 የመንግስት ተቋማት ውድመት የደረሰባቸው ሲሆን ይህን መልሶ ለማቋቋምም በዞኑ ስር ካሉ ነዋሪዎች 16 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን የባሌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አሊ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ አሁን ላይ የወደሙ 80 የመኖሪያ ቤቶች ተሰርተውና ተጠግነው መጠናቀቃቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ከዚህ ባለፈም ሆቴሎች በህዝብ ተሳትፎ እየተገነቡ መሆኑን በመጥቀስም የወደሙ የመንግስት ተቋማት በተመሳሳይ በህዝቡ ተሳትፎ ይገነባሉ ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ የተመራው ልኡክ በአርሲ ዞን ሌሞና ቢልቢሎ ወረዳ የገብስ፣ የስንዴ እና የባቄላ የክላስተር ማሳን ጎብኝተዋል።
በወረዳው 57 ሺህ 789 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በገብስ እና በባቄላ መሸፈኑን እና ከዚህ ውስጥ 20 ሺህ 879 ሄክታር መሬት የተሸፈነው በክላስተር መሆኑን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙዘይን አማን ነግረውናል።
በማህበር ተደራጅተው በስራው ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችም ከዚህ ቀደም በተበታተነ መልኩ የነበረውን አሰራር ቀይረው በክላስተር መስራታቸው ስንዴ ባንድ ሄክታር 80 ኩንታል፣ ገብስ 70 ኩንታል እና ባቄላ 50 ኩንታል እንደሚያገኙ ተስፋን ሰንቀው እየሰሩ መሆኑን ለልዑኩ አስረድተዋል ።
በተመሳሳይ ዜና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከአሰላ ከተማና በዙሪያዋ ካሉ ወረዳዎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሴቶች ጋር በሰላም እና በልማት ዙሪያ ተወያዩ
በውይይቱ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች ማህበረሰብ ሰላሙን ለማስጠበቅ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሰላም ከራስ አልፎ በጎረቤት ብሎም በሀገር ከሌለ ምንም ሊኖር አይችልም ያሉት የአከባቢው ነዋሪዎችም ብሄርን ከብሄር ፣የአንዱን ሀይማኖት ተከታይ ከሌላው ጋር ለማጋጨት በሚሰሩ ፀረ ሰላም ሀይሎች ላይ መንግስት በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀውል።
የአርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ጀማል አልይም በዞኑ ካሉት 25 ወረዳዎችና ሶስት ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ በስምንት ወረዳዎች ጉዳት መድረሱን እና ይህንን ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 1 ሺህ 750 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል የማጥራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም ማንም ሰው ከህግና ከህዝቡ በላይ ባለመሆኑ ህግን ተላልፈው ሀገርን ለማፈራረስ የሚሰሩ ሀይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በጉዳቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ረገድም መንግስት እንደሚሰራና መልሶ በማቋቋም ሂደቱም በተቀናጀ መልኩ ህዝቡ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራቸው ሰፋፊ የልማት ስራዎችም ውጤታማ እንዲሆኑ ህዝቡ የራሱንና የአከባቢውን ሰላም በመጠበቅና ከመንግስት ጋር ሆኖ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል።
የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዲሟላላቸው ለጠየቁት ጥያቄም ለአከባቢው ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመፍታት ከ800 ሚሊየን ብር በላይ ተመድቦ እየተሰራ መሆኑንና በንግድና በጤና ተቋማት ረገድም የክልሉ መንግስት ከዞንና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን እንደሚሰራ አንስተዋል።
በትዝታ ደሳለኝ

