Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሀገርን ብልጽግና የሚያረጋግጥ ገዢ ትርክት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገርን ብልጽግና የሚያረጋግጥ የወል ትርክት ለመገንባት በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ።

በኢትዮጵያ የጋራ ብሄራዊ ትርክቶችን ለመቅረጽ ያለመ ሀገር አቀፍ ጉባዔ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ እና በሕብረ ብሔራዊነት የተቃኘ አሰባሳቢ ትርክት መገንባት አስፈላጊ ነው።

በዘመናት የተዘሩ ከፋፋይ ትርክቶች የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ ሲጥሉ እንድነበር አስታውሰው÷ ይህንን የሚያስቀርና የሀገርን ብልጽግና የሚያረጋግጥ የጋራ ትርክት ለመገንባት በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።

እየተገነባ የሚገኘው የወል ትርክት ትናንትን የሚወቅስ ሳይሆን ዛሬን የተሻለ ለማድረግ እና ነገን በተስፋ ለመትለም የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ትውልዱ በወል ትርክት ዙሪያ ያለውን ግንዛቤና መረዳት ለማሳደግ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

ለገዢ ትርክት ዕውን መሆን የሐይማኖት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን እና መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ሁሉም ኃላፊነት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው÷ እንደ ሀገር ለአሰባሳቢ ትርክት የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉን አሰባሳቢ የወል ትርክት መገንባት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና መሠረት መሆኑን ብልጽግና ፓርቲ በጽኑ እንደሚያምን አውስተዋል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግም በኦሮሚያ ክልል በዕለት ተዕለት ሥራዎች ውስጥ የወል ትርክትን ለማንጸባረቅ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

በአንዱዓለም ተስፋዬ

Exit mobile version