Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ማህበረሰቡ በመረጠው የፍትህ ስርዓት እንዲዳኝ ለማስቻል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የክልሉ ማህበረሰብ በመረጠው የፍትህ ስርዓት እንዲዳኝ ለማስቻል እየተሰራ ነው አለ።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ ህዝቡ ፍትህ እንዲያገኝ አማራጭ የፍትህ ስርዓቶችን ለመዘርጋት ትኩረት ተሰጥቷል።

ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች ህዝቡ ፍትህ እንዲያገኝ እያስቻሉ ለዘመናት መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ለባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች አበርክቶ እውቅና መስጠት ይገባል ብለዋል።

መንግሥት ለባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች እውቅና በመስጠት እንዳይበረዙና እንዳይደበዝዙ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡ በመረጠው የፍትህ ስርዓት እንዲዳኝ ለማስቻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቶች በተጓዳኝ መጠቀም የዳኝነት ስርዓቱን ተደራሽነት ለማስፋት ፍትህንም በፍጥነት ለማረጋገጥ እድል የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

ባለፈው ታሕሣሥ ወር ባህላዊ አለመግባባቶችን የመፍቻ ሥርዓቶች ሲተገብሩ የነበሩ 15 ባህላዊ ተቋማት የባህል ፍርድ ቤት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ እውቅና ተሰጥቷቸው በይፋ የሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ማካሄዳቸው ይታወሳል።

የባህል ፍርድ ቤትነት ዕውቅና የተሰጣቸው ሽምግልና፣ አበጋር፣ ⁠ረከቦት፣ ዱለት፣ ⁠አማሬ ቁና፣ አውሳይድ ፣ ⁠ጎራው አባ አሊ፣ ⁠ስምንቱ ማይ ቤት፣ ዘወልድ፣ መዛርድ፣ ክፍሎ፣ ⁠ሰንዬሰገድ፣ ⁠አባሀጋ፣ ⁠ዙፋን ዋልዋጅ እና ሰባቱ ከዘራ ናቸው።

በሙሉቀን አበበ

Exit mobile version