Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፓርቲያችን የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫ ውጤታማ እየሆነ ነው – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፓርቲያችን የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አቅጣጫ ውጤታማ እየሆነ ነው አሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ።

በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የፓርቲ አመራሮች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምስራቅ ጉራጌ ዞን የልማት ስራዎችን ተመልክቷል።

አመራሮቹ በቡታጅራ ከተማ የአቮካዶ ዝርያ ማሻሻያ ማዕከል፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክት፣ ቀሸት ንብ ማነብ ስራ ማህበር እና ደስታ ጋርመንትን ምልከታ አድርገዋል።

አቶ አደም በዚህ ወቅት÷ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኮሪደር ልማትና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተሰሩ ባሉ ስራዎች የፓርቲው እሳቤዎች ገቢራዊነቱ በሁሉም መስክ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ድርጅቶችን መመልከት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደረገች ላለችው ሽግግር ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሀገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል ማለታቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

የብልፅግና ፓርቲ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ከነገ ጀምሮ በሆሳዕና ከተማ እንደሚካሄድም ተገልጿል።

Exit mobile version