አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት 263 ነጥብ 16 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አልሚዎች 143 ሺህ ሄክታር የመሥሪያ ቦታ ተሰጥቷል አለ የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ አሕመድ ኢድሪስ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ በክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት ምህዳር ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው።
በዚህም መሰረት ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ህጎችና አሰራሮችን በማሻሻል አስቻይና ተደራሽ ሥርዓቶች እየተዘረጉ ነው ብለዋል።
የክልሉን የኢንቨስትመንት እምቅ አቅም በመለየት ለኢንቨስትመንት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለአብነትም ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ተዘጋጅቶ ለባለሃብቶች ክፍት መደረጉን ጠቁመዋል።
ለኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚሆን መሬት በቅንጅትና በስፋት ተዘጋጅቷል ያሉት ኃላፊው፥ በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
በበጀት ዓመቱ የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ሁለት ዙር መድረኮችን በማካሄድ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን አንስተዋል።
በዚህም በጥቅምት ወር የመጀመሪያ መድረኩ 90 ነጥብ 618 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 3 ሺህ 163 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።
ባለፈው ወር ባካሄደው 2ኛ መድረኩ 172 ነጥብ 54 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 5 ሺህ 158 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ በመወሰን ስራ ላይ እንዲውሉ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ እንደሚሰማሩ ነው የገለጹት።
ባለብቶቹ ደንብና መመሪያ በማክበር በተቀመጠላቸው ጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡን አስገንዝበዋል።
በዚህ ውሳኔ ለቡና ልማት ኢኒሼቲቭ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማዘጋጀት ለ148 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በቡና ልማት ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ ፍቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት።
በአጠቃላይ የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ በሁለት ዙር ባካሄደው መድረክ 8 ሺህ 321 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ አጽድቋል፡፡
ለእነዚህ 263 ነጥብ16 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ፕሮጀክቶች 143 ሺህ ሄክታር መሬት ለየመስሪያ ቦታ የተሰጠ ሲሆን፥ ፕሮጀክቶቹ በሙሉ አቅማቸው ወደ ምርትና አገልግሎት ሲገቡ ከ691 ሺህ 126 በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።
በመላኩ ገድፍ

