Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የቱሉ አራራ ሞዴል መንደርን በሌሎች አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ

አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የቱሉ አራራ ሞዴል መንደር በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የክረምት በጎ አድራጎት መርሐ ግብርን ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረውን የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደር ባለፈው ሳምንት በይፋ መመረቃቸው ይታወሳል፡፡

የተቀናጀ ሞዴል መንደሩ 35 አባወራዎችን የያዘ ሲሆን፥ የገጠርና ከተማ ልማትን በማቀናጀት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ታቅዶ የተገነባ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

በቱሉ አራራ ሞዴል መንደር የሚኖሩ ነዋሪዎች የጓሮ አትክልት እንዲያለሙና በቀን 15 እስከ 20 ሊትር ወተት መስጠት የሚችሉ ላሞችን እንዲያረቡ በማመቻቸት የከተማ ግብርና ተግባራዊ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

በሚያመርቷቸው ምርቶች ለራሳቸው የምግብ ፍጆታ ከመጠቀም ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉንም አስረድተዋል።

ዜጎችን በማስተባበርና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኛ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም ከለውጡ ወዲህ በተሰሩ የበጎ ፍቃድ ስራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የእርስ በእርስ መቀራረብ ጨምሯል ነው ያሉት።

ከተሞችን በማዘመን ስራ በተለይ በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ ከ70 በላይ ከተሞች ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን፥ ይህም ከተሞችን ይበልጥ ከማዘመን ባለፈ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የገጠር ኮሪደር ልማት በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ የቱሉ አራራ የተቀናጀ ሞዴል መንደርን በሌሎች አካባቢዎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በነፃነት ጸጋይ

Exit mobile version